
በኦገስት የመጨረሻው አሥራ አንድ ቀናት ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ ይሄዳሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ ምዕራብ፣ መካከለኛው፣ ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት ይኖራቸዋል። ስለሆነም እርጥበታማው የአየር ሁኔታ በተለይም በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅ እና መካከለኛዉ የሀገራችን አከባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸዉ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በሌላ በኩል በመካከለኛው፣ በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገራችን አከባቢዎች ላይ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩት የአየር ሁኔታ ክስተቶች ላይ በመነሳት ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡