
በጁን የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ለዝናብ መፈጠር አስዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በተለይም በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖራቸው የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም እርጥበታማው የአየር ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገራችን አከባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸዉ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በተጨማሪም አልፎ አልፎ በውሃ አካላትና በከባቢ አየር ውስጥ ከሚጠናከሩት የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ላይ በመነሳት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ እና በመካከለኛወ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 ሚ.ሜ በላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡