
በኦገስት የመጀመሪያው አስር ቀናት ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ ይሄዳሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ መካከለኛው፣ ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ስለሆነም እርጥበታማው የአየር ሁኔታ በተለይም በምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ እና መካከለኛዉ የሀገራችን አከባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ በብዙ ቦታዎቻቸው ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ይኖራቸዋል፡፡ በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅ እና በደቡብ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸዉ አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ፡፡