
እ.ኤ.አ ከኤፕሪል 1 እስከ ሜይ 31/2024 የሚኖረው የአየር ጠባይ አዝማሚያ በውሃው ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተፅዕኖ
በኤፕሪል ወር በኦሞጊቤ፣ ስምጥሸለቆ፣ የላይኛውና የመካከለኛው አዋሽ፣ አባይ፣ ገናሌዳዋ፣ የላይኛው እና የመካከለኛው ተከዜ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ እንዲሁም አፋር ደናከል ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እርጥበት እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል፡፡ በሜይ ወር በአብዛኛው ባሮ አኮቦ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ዋቤ ሸበሌ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ በመካከለኛው እና በታችኛው አባይ እና በላይኛው አዋሽ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እርጥበት እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚኖረው የትንበያ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በአንጻሩ ግን አልፎ አልፎ ሊኖር ከሚችለው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ በተለይም በከተሞች አካባቢና ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ ተፋሰሶች እና ንዑስ ተፋሰሶች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍም ሆነ የወንዞች ሙላት በማስከተል በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አስፈላጊውን የጥንቃቄ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡