በቀሪዎቹ ሁለት ወራት በአብዛኛዎቹ የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ ወቅታዊው ዝናብ ቀጣይነት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን፤ በአብዛኛዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖርና በጥቂት ስፍራዎችም ላይ ከባድ ዝናብ አልፎ አልፎ በሚኖሩት ቀናቶች የመኖር ዕድል አለው። በሌላ በኩል በሜይ ወር ከክረምት ዝናብ መጀመር ጋር ተያይዞ ምዕራባዊው የሀገሪቱ አጋማሽ የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት ሊኖራቸው እንደሚችል ይጠበቃል። በአጠቃላይ በቀሪዎቹ የበልግ ወራት አሁን በመታየት ላይ ካለውና ወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ ሊኖር እንደሚችል በሚጠበቀው ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የትሮፒካል ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት አንጻር መደበኛና ከመደበኛ በላይ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚችል ግንዛቤ ተወስዶበታል።