የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የአየር ጠባይ ማዕቀፍን በክልል ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የምክክር መድረክ አዘጋጀ
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የአየር ጠባይ ማዕቀፍን በክልል ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ከሁሉም ክልል መንግስታት የውሃ፣ የአደጋ ስጋት፣ የግብርና፣ የጤና እና የአካባቢ ጥበቃ የቢሮ ሃላፊዎች እንዲሁም የክልሎቹ ፕሬዝዳንቶችና ተወካዎቻቸው በተገኙበት በአዳማ ከተማ ሐይሌ ሪዞርት ከጥቅምት 17-18 ቀን 2016 ዓ.ም መድረክ አዘጋጅቷል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ሃብታሙ ኢተፋ መድረኩን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት አገራችን በተለያየ ጊዜ በሁለት የተለያዩ የአየር ጠባይ ተፅእኖዎች ስር ማለትም በድርቅና በጎርፍ የምትጠቃ በመሆኗ ኢንስቲትዩቱ በመደበኛ ደረጃ ከሚሰጠው ትንበያ በተጨማሪ ታች ያለውን ህብረተሰብ የመረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ስርአት ዘርግቶ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
ለመድረኩ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተርና በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት የሆኑት አቶ ፈጠነ ተሾመ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቋቋመውን የዓለም አቀፍ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማዕቀፍ መመሪያ መሠረት በማድረግ ብሔራዊ የአየር ጠባይ አገልግሎት ማእከል በአገራችን መጀመሩን አስታውሰው ይህ ማዕቀፍ የአየር ጠባይ አገልግሎቶች በዓይነት፣ በብዛት እና በጥራት የተሻሉ እና ተጠቃሚዎች በየደረጃው ውሳኔ ለመስጠት በሚያስችላቸው መንገድ ተዘጋጅተው እንዲሠራጩና ተግባር ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችል አሠራርን አሰራር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ለሁለት ቀን በሚቆየው መድረክ ላይ ከክልሎች ጋር የጋራ መግባባት ከተደረሰ በኋላ የጋራ የስራ ስምምነት ሰነድ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡