ኢንስቲትዩቱ በቀሪዎቹ የክረምት ወራት መደበኛ የዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ሐምሌ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተርና በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለፁት ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደነበራቸውና ወቅቱ በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባህር ወለል ሙቀት
ከመደበኛ በታች መቀዝቀዝ (ENSO- LA NINA) እንዲሁም የሰሜናዊ ህንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባህር ወለል ሙቀት መጠን (Neutral IOD) ሆኖ መቆየቱ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው ገልፀዋል ፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም በቀሪዎቹ የክረምት ወራት ማለትም በነሀሴና በመስከረም ወራቶችም የክረምት ዝናብ
በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ በተሻለ ጥንካሬ እንደሚቀጥል በመግለጫቸው የተናገሩ ሲሆን ህብረተሰቡ በቀሪ የክረምት ወራቶች የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ
ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባትና የሚገኘውን ከመደበኛ በላይ የሆነ የዝናብ መጠንና ስርጭት በአግባቡ በመጠቀም በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።