ለአየር ንብረት ለውጥ በትብብር መሰራት እንዳለበት ተገለፀ

20 Jan, 2025 News

photo_2025-01-23_15-30-31

69ኛው የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የአየር ጠባይ ትንበያ ፎረም በአዲስ አበባ -ኢትዮጵያ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በመድረኩን የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ የአየር ንብረት ለውጥ በድንበር የማይወሰን መሆኑን በመግለፅ ሁሉም የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት አባል አገራት በቅንጅትና ትብብር መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በስፋት እየሰራች መሆኑን ገልፀው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን በመስራት ለግብርናው፣ ለውሃው፣ ለአደጋ ስጋቱ እንዲሁም ለጤናው የሚያስከትለውን ተፅእኖ በመገምገም እንደ ምስራቅ አፍሪካ ክልል መደረግ የሚገባውን ጥንቃቄ ማድረግና ወደ አገርም በማውረድ አገራዊ የወቅት ትንበያ በመስጠት በአየር ንብረት ለውጥ የሚመጣውን አደጋ መቀነስ እንደሚገባ አሳሰበዋል፡፡

የእለቱ የክብር እንግዳ በሚንስቴር ድኤታ ማእረግ የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር የሚንስትሩ አማካሪ አቶ ሞቱማ መቃሳ መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረው ተፅእኖ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካ ቢሆንም ለአፍሪካ ደግሞ ጫናው ከፍ ያለ በመሆኑ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት የአየር ጠባይ ትንበያ ማእከል ተጠናክሮ መስራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

ፎረሙ እስከ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ- ስካይ ላይት ሆቴል እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡