ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደሩ የአየር ሁኔታና ጠባይ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን ለመስራት የሚያግዝ ፕሮጀክት በሚዛን አማን

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለአርብቶ አደርና ለከፊል አርብቶ አደሩ የአየር ሁኔታና ጠባይ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን ለመስራት የሚያግዝ ፕሮጀክት ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል በሚዛን አማን ከተማ ይፋ አደረገ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተርና በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ መድረኩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት ኢንስቲትዩቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን ሰብስቦ ተደራሽ ለማድረግ ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን ለማስፋፋት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አርብቶ አደርና ቆላማ አካባቢ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምሩ ቦኒ በዘርፉ የነበረውን የተደራሽነት ችግር ለመቅረፍ ኢንስቲትዩቱ ላሳየው ቁርጠኝነት በማመስገን የአየር ንብረት መለዋወጥ የወቅቱ የአገር ወይም የክልል አሳሳቢ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የቤተሰብ ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ ኢንስቲትዩቱ የሚሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምክረ ሀሳብ ለአካባቢው ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ጠቁመዋል።
በአርብቶና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ክልል አምስት ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ከፕሮጀክቱ አስተባባሪ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡